ለባለአክሲዮኖች 4ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የቀረበ የተቋሙ 2025/2026 የሂሳብ ዓመት የዳይሬክተሮች ቦርድ የስራ አፈፃፀም ሪፖርት

መግቢያ

የተከበራችሁ የአቦል ቡና ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም አ.ማ. ባለአክሲዮኖች፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተወካዮች፣ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ተወካዮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላችሁ ክቡራን እንግዶች፣ ክቡራንና ክቡራት እንኳን ለአቦል ቡና ማይክሮ ፋይናንስ አ.ማ 4ኛ መደበኛ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ በሰላም አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ! 

አቦል ቡና ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም አ/ማ በአዋጅ ቁጥር 626/2001 (በአዋጅ ቁጥር 1164/2012 እንደተሻሻለ) ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እ.ኤ.አ ኤፕሪል 16/2024 አነስተኛ የፋይናንስ ስራ ፈቃድ ቁጥር 066/2024 አግኝቶ ስራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሰረት ለተከበረው ጠቅላላ ጉባኤ እ.ኤ.አ ከጁላይ 1 ቀን 2025 እስከ ጁን 30 ቀን 2026 ድረስ ያለውን የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት እንደሚከተለው በዝርዝር አቀርባለሁ፡፡ 

  1. የኦፕሬሽን ሥራ አፈፃፀም በተመለከተ

በሂሳብ ዓመቱ በዓለም አቀፍ እና በሀገር ደረጃ በርካታ ተግዳሮቶች የነበሩ ቢሆንም አቦል ቡና ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም እነዚህን ተግዳሮቶች በመቋቋም ለተጠናቀቀው ሂሳብ ዓመት የተቀመጡ ዓላማዎችን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን የአፈጻጸም ዝርዝሩም እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

1.1 አዳዲስ ደንበኞች ምልመላ እና ቅርንጫፍን ማስፋፋት በተመለከተ፣

አቦል ቡና ማይክሮ ፋይናንስ በአዲስ አበባ ከተማ ደንበል እና ጎፋ እንዲሁም በአማራ ክልል ደብረብርሃን፣ ባህርዳር፣ ጫጫ እና ደብረማርቆስ በጠቅላላ ስድስት ቅርንጫፎችን በመክፈት ለደንበኞች ተደራሽ ለመሆን ችሏል:: በዚህም መሰረት በሂሳብ ዓመቱ 4,981 የቁጠባ ደንበኞችን እና 359 ተበዳሪዎችን በአጠቃላይ 5,340 ደንበኞችን ማፍራት ችሏል፡፡ ይህ አጠቃላይ የደንበኛ ቁጥር ባለፈዉ ዓመት ከነበረዉ 2,282 የደንበኛ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር የ133.98% እድገት አሳይቷል፡፡ ከእቅድ ከተያዘዉ 5,640 ጋር ሲነፃፀር ደግሞ የዕቅዱን 94.68% አሳክቷል።

  1. የተቀማጭ ገንዘብ አፈጻጸም በተመለከተ፤

በተጠናቀቀው የሂሳብ ዓመት የማይክሮ ፋይናንሱ አጠቃላይ ተቀማጭ ሒሳብ ብር 89.1 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ ብር 8.3 ሚሊዮን ብር (9.32%) የግዴታ ቁጠባ፣ ብር 80.8 ሚሊዮን (90.68%) ደግሞ የፍቃደኝነት ተቀማጭ ነዉ፡፡ ይህም የቁጠባ መጠን በእቅድ ተይዞ ከነበረዉ ብር 91.7 ሚሊዮን ጋር ሲነፃፀር የዕቅዱን 97.16% ያሳካ ሲሆን፤ ካለፈዉ የሂሳብ ዓመት ብር 29.7 ሚሊዮን አፈጻጸም ጋር ሲነፃፀር 300% እድገት ያሳያል።

  1. የብድር ስርጭት አፈፃፀም (Loan Disbursement) በተመለከተ፤

ጁን 30/2026 በተጠናቀቀው ሂሳብ ዓመት ብር 81.6 ሚሊዮን ብድር ለ271 (ሁለት መቶ ሰባ አንድ) ተበዳሪዎች ተሰራጭቷል፡፡ ይህም በዕቅድ ተይዞ ከነበረዉ ብር 100 ሚሊዮን አንፃር 81.6% የተፈጸመ ሲሆን፤ ካለፈዉ ዓመት የብር 41.6 ሚሊዮን አፈፃጸም አንጻር ደግሞ 96.15% እድገት ያሳያል።

  1. የብድር ቀሪ ሂሳብን (Loan Outstanding) በተመለከተ

በተጠናቀቀው የሂሳብ ዓመት ከ359 ደንበኞች ላይ ብር 79.1 ሚሊዮን የብድር ቀሪ ሂሳብ (Loan Outstanding) የሚገኝ ሲሆን፤ ይህም በዕቅድ ተይዞ ከነበረዉ ብር 101.8 ሚሊዮን አንፃር የዕቅዱን 77% አሳክቷል፡፡ ካለፈዉ ዓመት የብር 35.6 ሚሊዮን አፈፃፀም አንጻር ደግሞ 122.19% እድገት ያሳያል።

1.5 የብድር ስርጭት ጥራትን (Portfolio Quality) በተመለከተ፤

በሂሳብ ዓመቱ በተቋሙ ውስጥ ምንም ውዝፍ ብድሮች እንዳይኖሩ ለማድረግ በብድር አመላለስ እና ጥራት ላይ የዳይሬክተሮች ቦርድ በየወሩ እና በየሩብ ዓመቱ እየገመገመ ለተቋሙ ሥራ አመራር አካላት አቅጣጫ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡በየደረጃው ያለው የብድር ስርጭት ኮሚቴም ደንበኞች ብድር ከመውሰዳቸው በፊት የሚፈለግባቸውን መስፈርቶች ማሟላታቸውን እና ለብድር አመላለሱ በቂ ዋስትና ስለማቅረባቸው ተገቢውን ክትትልና የማያቋርጥ ድጋፍ በማድረግ የተቋሙን የብድር ጥራት ለመጠበቅ ተችሏል፡  

  1. የፋይናንስ ሥራ አፈፃፀምን በተመለከተ፤

የሂሳብ ዓመቱ የፋይናንስ ሪፖርት በዓለም አቀፍ የሂሳብ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃዎች (IFRS) መሠረት የተዘጋጀ ሲሆን፤ ዝርዝሩ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ 

2.1 ገቢ   

በተጠናቀቀው የሂሳብ ዓመት የተቋሙ አጠቃላይ ገቢ ብር 24.3 ሚሊዮን ሲሆን፤ በዝርዝር የገቢ ርዕስ ሲታይም ከብድር ወለድ ብር 19.3 ሚሊዮን፣ ከአገልግሎት ክፍያ ብር 2.6 ሚሊዮን እንዲሁም ከባንክ ተቀማጭ ወለድ እና ከሌሎች ምንጮች ብር 2.4 ሚሊዮን የተገኘ ገቢ ነው፡፡ ይህ አጠቃላይ ገቢ በእቅድ ከተያዘው ብር 30.5 ሚሊዮን አንፃር 79.67% የተፈጸመ ሲሆን፤ ካለፈዉ የሂሳብ ዓመት ብር 9.4 ሚሊዮን አፈፃጸም ጋር ሲነፃፀር ደግሞ 158.51% እድገት ያሳያል፡፡

2.2 ወጪ

በተጠናቀቀዉ ሂሳብ ዓመት አጠቃላይ ወጭ ብር 20.9 ሚሊዮን ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፤በወጭ ዝርዝር ሲታይም ለአስተዳደራዊ እናለጠቅላላ አገልግሎት ማለትም ለሠራተኛ ደመወዝ እና ጥቅማጥቅም ብር 7.8 ሚሊዮን፣ለቢሮዎች ኪራይ ብር 2.1 ሚሊዮን፣ ለቋሚ ንብረቶች የእርጅና ቅናሽ ብር 549,543፣ለቁጠባ ወለድ ብር 6.2 ሚሊዮን፣ እንዲሁም ለሌሎች ኦፕሬሽናል ሥራ ማስኬጃ ወጭ ብር 3.7 ሚሊዮን ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

  1. ትርፍ እና ኪሳራ በተመለከተ፤

ተቋሙ በተጠናቀቀዉ የሂሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ብር 3.2 ሚሊዮን ትርፍ በማስመዝገብ በእቅድ ተይዞ ከነበረዉ የብር 2.7 ሚሊዮን በ18.52% ብልጫ ያለው አፈጻጸም አስመዝግቧል፡፡ ካለፈዉ የሂሳብ ዓመት ብር 721,677 አፈፃጸም ጋር ሲነፃፀር ደግሞ 343.41% እድገት ያሳያል።

  1. የሀብት እና ዕዳ መግለጫን በተመለከተ፤
    1. የሀብት መግለጫ

የተቋሙ ጠቅላላ ሀብት ከባለፈዉ የሂሳብ ዓመት ከነበረበት ብር 72.5 ሚሊዮን በ2025/2026 ወደ ብር 147.4 ሚሊዮን አድጓል፡፡ ይህም የ103.31% የሀብት እድገት አሳይቷል። በሂሳብ ዓመቱ የተሻለ የብድር ሥርጭት መድረጉ ለጠቅላላ ሀብት እድገቱ ዋንኛው ምክንያት ሲሆን፤ብር 79.1 ሚሊዮን የሚሆነው በደንበኞች እጅ የሚገኝ የብድር ቀሪ ሂሳብ የጠቅላላ ሀብቱን 53.66% ድርሻ ይዟል።

  1. የዕዳ መግለጫ

ጁን 30/2026 ላይ የተቋሙ ጠቅላላ ዕዳ ብር 93.3 ሚሊዮን ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ ብር 89.1 ሚሊዮን የደንበኞች ቁጠባ የጠቅላላ ዕዳውን 95.50% ድርሻ ይዟል፡፡ ቀሪው 4.50% ድርሻ የያዘው ብር 4.2 ሚሊዮን ደግሞ የቁጠባ ወለድ ክፍያ፣ለመንግስት የሚከፈል የግብር ክፍያዎች እንዲሁም የሰራተኞች የአመት እረፍት ዕዳዎች ናቸው።

2.4.3 ጠቅላላ ካፒታል

የተቋሙ ጠቅላላ ካፒታል 54.1 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ 50.8 ሚሊዮን ብር የተቋሙ የአክሲዮን ክፍያ(Paid Up Capital) ሲሆን 93.90% ድርሻ ይዟል፡፡ ቀሪው 6.10% ድርሻ የያዘው ብር 3.3 ሚሊዮን ደግሞ የሂሳብ ዓመቱ ያልተከፋፈለ ትርፍ እና የሕጋዊ መጠባበቂያ ነው።

  1. የሰው ኃይል አደረጃጀትን በተመለከተ፤

በሂሳብ ዓመቱ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች ዋነኛው ተቋሙን ብቃት ባለው የሰው ኃይል ማደራጀት ነው፡፡ በዚህም መሠረት በተለያዩ የሥራ መደቦች ላይ 32 ሠራተኞች ለመቅጠር የተቻለ ሲሆን፤ከጠቅላላ አዲስ ቅጥር ሠራተኞች 59.38% ድርሻ የያዘው 19 ሠራተኞች ሴቶች ቀሪዎቹ 13 ደግሞ ወንዶች ናቸው፡፡ የሰው ኃይሉን አቅም በመገንባት ውጤታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ እና በብቃት ለመሥራት የሚረዱ የተለያዩ ሥልጠናዎች ለሠራተኞች ተሰጥቷል፡፡ የተቋሙን ትርፋማነት ማሳደግ ወሳኝ በመሆኑ የሠራተኞችን የመፈጸም አቅም በማሳደግ፣ ዕቅድ መስጠት እና አፈፃፀማቸውን በወቅቱ የመገምገም ሥራ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል::

  1. ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር

ተቋሙ ከካስቀመጣቸው ዓላማዎች አንዱ ማኅበራዊ ኃላፊነት መወጣት በመሆኑ በሂሳብ ዓመቱ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ለሚገኙ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸዉ የህብረተሰብ ክፍሎች በገና በዓል ወቅት ድጋፍ አድርጓል።

  1. ተቋሙን በቴክኖሎጂ ከማዘመን አንጻር

ከአቦል ቡና ማይክሮ ፋይናንስ ዓላማዎች አንዱ ዘመኑ ባፈራቸው ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎት መስጠት ሲሆን፤ ይህን ዓላማውን እውን ለማድረግ ከ45 ማይክሮ ፋይናነስ ጋር በጋራ በመሆን ኢት ኢንክሉሲቭ ፋይናንስ ቴክኖሎጅ አ.ማ ድርጅት የጋራ የኮር ባንኪንግ ሲስተም በመግዛት እየሰራ ይገኛል እንዲሁም ሞባይል ባንኪንግ እና ኢንተርኔት ባንኪንግ ለመጠቀም በዝግጅት ላይ ነው። 

  1. የሥራ ዋጋ እና የጥቅማ ጥቅም ክፍያዎች

በሂሳብ ዓመቱ ውስጥ ለዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት እና ለዋና ሥራ አስፈፃሚ የተከፈሉ ክፍያዎችን በተመለከተ በንግድ ሕጉ ቁጥር 314 መሰረት ዝርዝሩ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

  1. ለሰባት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ለ2025/2026 ሂሳብ ዓመት የተከፈለ ወርሃዊ አበል ብር 840,000፣
  2. ለዋና ሥራ አስፈፃሚ በሂሳብ ዓመቱ ደመወዝና ጥቅማ-ጥቅም የተከፈለ ብር 1,114,380 እንዲሁም በኩባንያው መመሪያ መሠረት በየወሩ ከደመወዛቸው እየተቆረጠ ተመላሽ የሚሆን ለአስቸኳይ ጊዜ ብድር ብር 250,000 ተሰጥቷል፡፡
  1. የተከበራችሁ የኩባንያው ባለአክሲዮኖች

በሂሳብ ዓመቱ የዳይሬክተሮች ቦርድ ከላይ በዝርዝር ከተጠቀሱ አበይት ጉዳዮች በተጨማሪ ልዩ ልዩ ተግባራት እንዲከናወኑ እና ኩባንያው ውጤታማነቱን አስጠብቆ እንዲቀጥል የሚያስችል አመራር ለማኔጅመንቱ በመሰጠት እና በራሱ በመፈጸም የሚከተሉትን ዋና ዋና ተግባራት አከናውኗል፡

  1. የ3ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ እና 1ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤዎችን በስኬታማነት በማካሄድ የጉባኤዎቹን ቃለ-ጉባዔዎች እንዲፀድቁ ተደርጓል፡፡
  2. የዳይሬክተሮች ቦርዱ በተቋሙ ውስጥ የኮርፖሬት አስተዳደር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማስቻል በየ15 ቀኑ በሚያደርገው ስብሰባ የተቋሙ ስራዎች አግባብነት ካላቸው ሕግና መመሪያዎች መሰረት መፈጸማቸውን በመቆጣጠር፤ ማኔጀመንቱ ከአጋር አካላት ጋር ለውን ትብብርና ቅንጅት አንዲያጠናክር ተገቢ የሆነ አቅጣጫና ድጋፍ በማድረግና ሌሎችም ተግባራት ተከናውኗል፡፡   
  3. የተቋሙን የሥራ አፈጻጸም ውጤት በየሩብ ዓመቱ በቦርዱ በጥልቀት ተገምግሞ ተገቢውን የማስተካከያ እርምጃና አመራር ተሰጥቷል፣ 
  4. የተቋሙን ሰነደ ሙዓለ ነዋዮች እና ደንበኛ ሳቢ መግለጫ (prospectus) ከባለስልጣኑ ፈቃድ በተሰጣቸው ትራንዛክሽ አድቫይዘር በማዘጋጀት በገለልተኛ የሕግ አማካሪ እና የውጭ ኦዲተር በማረጋገጥ በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ለማስመዝገብ በማኅበራችን በኩል የተመረጡ አማካሪዎችን ከሌሎች አቻ ተቋማት ጋር በጋራ በመቅጠር በአነስተኛ ወጭ የምዝገባ ሂደቱ የመጨረሻ ምዕራፍ እንዲደርስ ተደርጓል፡፡ቀሪ ስራዎችም በአጭር ጊዜ ተሰርተው ምዝገባው የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ 
  5. በዋጋ ንረት እና በነዳጅ ከፍተኛ ጭማሪ መንስኤ በአገሪቱ በተፈጠረው የመሰረታዊ ፍላጎቶች መናር በሠራተኛው ላይ ያስከተለውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና በተወሰነ ደረጃ በማስታገስ የተቋሙን ምርታማነት ለማስቀጠል የኑሮ ውድነት ማካካሻ ተደርጓል፡፡
  6. የተቋሙን የ2026/2027 የሂሳብ ዓመት የሥራ እቅድና በጀት በወቅቱ ቀርቦ እንዲጸድቅና ወደ ስራ እንዲገባ ተደርጓል፡፡
  1. ያጋጠሙ ዋና ዋና ተግዳሮቶች የሚከተሉት ናቸዉ፡፡
  • በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ መሰረት ተቋሙ ለአንድ ደንበኛ የሚያበድረገው የብድር ጣሪያ መጠን የካፒታሉን 1 በመቶ ብቻ በመሆኑ፤
  • በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶ በገበያ ማስፋት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ፤
  • በአገሪቱ በተከሰተው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት መንስኤ በተበዳሪዎች የተሻለ የማበደር አቅም ያላቸው ተቋማትን የመምረጥ አዝማሚያ መታየቱ፤  
  • በተቋማቱ ዉስጥ ተገቢ ያልሆነ ዉድድር መኖሩ፤ 
  • በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን የምዝገባ ሂደት ፈጥኖ አለመጠናቀቁ በአክሲዮን ሽያጭ ላይ ገደብ ማሳደሩ፤
  1.  የተቋሙ የወደፊት የትኩረት አቅጣጫዎች
  • የካፒታል ገበያ ባለስልጣን የምዝገባ ስርዓት ፈጥኖ በማጠናቀቀ የተቋሙን ካፒታል ማሳደግ፤ 
  • የተቀማጭ ሀብት (Resource moblization) በተለይም ቁጠባ መር ስራዎችን በስፋትና በተቀናጀ ሁኔታ መስራት፤
  • በአዋጭነት ጥናት ላይ የተመሰረተ የቅርንጫፍ መክፈት እና የገበያ ድርሻን ማስፋት/ማሳደግ፤
  • የተቋሙን መልካም ስምና ገጽታ መገንባት፤ 
  • በሰው ኃይል ልማት ላይ አተኩሮ በመስራት እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት በአገልግሎት ጥራት እና ተደራሽነት ላይ ትኩረት መስጠት፤
  • በእዉቀታቸዉና በገንዘባቸዉ ተቋሙን ሊያግዙ ከሚችሉ ባለአክሲዮኖችም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አአካላት ጋር የአጋርነት እና አብሮ የመስራት ትስስርን ማጠናከር፤
  • የተቀመጡ ትኩረት አቅጣጫዎችን ለማስፈጸም ስልት ነድፎ በየጊዜው ክትትልና ድጋፍ በመስጠት ውጤታማነቱ ላይ አተኩሮ መስራት 
  1. 10.የትርፍ ክፍፍል 

ተቋሙ በተጠናቀቀው የሂሳብ ዓመት ከአጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ ከታክስ በፊት ብር 3,292,779.00 (ሦስት ሚሊዮን ሁለት መቶ ዘጠና ሁለት ሽህ ሰባት መቶ ሰባ ዘጠኝ ብር) ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን፤ ከእዚሁ ላይ ለታክስ፣ ለሕጋዊ መጠባበቂያ እና ለዳይሬክተሮች ቦርድ ዓመታዊ ክፍያ ተቀንሶ የሚገኘው የተጣራ ትርፍ ባለአክሲዮኖች ባላቸው የተከፈለ አክሲዮን መጠን እና አክሲዮኑ የተከፈለበትን ጊዜ በመውሰድ የሚሰራና ከተቋሙ የሰነደ ሙዓለ ነዋዩች ምዝገባ መጠናቀቅ በኋላ የሚከፋፈል ይሆናል፡፡

ማጠቃለያ

ከላይ የተጠቀሱት ተግዳሮቶች ቢኖሩም የዳይሬክተሮች ቦርድ፣ ማኔጅመንቱ እና መላው ሠራተኞች ተቀናጅቶ በመስራት በአደረጃጀት፣በሰው ኃይል ልማትና በቴክኖሎጂ በማስደገፍ፣ከአጋሮች ጋር ትብብር እና ቅንጅት በመፍጠር፣ በደንበኞች አገልግሎት ዘርፍ የታዩትን አመርቂ ሂደቶች በማጎልበት ረገድ በተነሳሽነት እየተሰራ የሚገኝ ሲሆን፤የተቋሙን ርዕይ እና ተልዕኮ ለማሳካት የተጀመሩ አስቻይ ሁኔታዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል ውጤታማ አፈጻጸም ለማስፈጸም በቁርጠኝነት እንደሚሰራም በዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፣በመላው ሠራተኛ እና በራሴ ስም ለማረጋገጥ እወዳለሁ።

የተከበራችሁ ባለአክሲዮኖቻችን በአክሲዮን ግዥ፣ በቁጠባ ማሰባሰብ እና በብድር ዘርፎች ያሳያችሁትን ያልተቋረጠ ድጋፍና ትብብር በማስቀጠል ለተቋማችን የተሻለ ወደፊት ስኬት ከጎናችን እንድትቆሙ እና የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድታበረክቱ አበክሬ እጠይቃለሁ።

በመጨረሻም በተጠናቀቀዉ በጀት አመት ተቋሙ ላስመዘገበዉ የላቀ ዉጤት የሁሉም ባለድርሻ አካላት አስተዋጽ ከፍተኛ ነዉ። በመሆኑም የዳይሬክተሮች ቦርድ ለባለአክሲዮኖች፣ ለደንበኞች፣ ባለድርሻ አካላት እና አጋሮቻችን፣ ለድርጅቱ ስራ አመራር እና መላው ሰራተኞች በራሴና በዳሬክተሮች ቦርድ ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡

አመሰግናለሁ

የአቦል ቡና ማይክሮ ፋይናንስ አክሲዮን ማኅበር

የዳይሬክተሮች ቦርድ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top